የቻይናው ካምፓኒ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የፈንጅ ማምከኛ መሳሪያዎችን አበረከተ

ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) –  የቻይና ትያንጂን ማይወይ ኢንተርናሽናል የግል ካምፓኒ በ22 ሚሊየን 8 መቶ 80 ሺህ ብር የሚገመቱ የፈንጅ ማምከኛ መሳሪያዎችን በዛሬው እለት ለፌዴራል ፖሊስ በድጋፍ አበርክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ለፀረ-ፈንጅ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት በተለያዩ መሰረተ ልማቶች እና ትላልቅ ተቋማት ላይ በማሰማራት በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደገፈ ፖሊሳዊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከፈንጅ ማምከኛ መሳሪያዎቹ በተጨማሪ በሰለጠኑ የፈንጅ አነፍናፊ ውሾች በመታገዝ ከፀረ-ፈንጅ ባለሙያዎች የተሰወሩ ነገሮችን የመለየት ስራ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር የፀረ-ፈንጅ መሳሪያዎቹ የፀረ-ሰላም ኃይሎችን እኩይ ተግባር ለመመከት እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን በመግለፅ ካማፓኒው ላበረከተው ድጋፍ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የፀረ-ፈንጅ ምክትል ዳይሬክቶሬትም መሳሪያዎቹን በአግባቡ በመጠቀም ለተፈለጉለት አላማ እንዲያውላቸው ኮሚሽነር ጄነራሉ ከአዳራ ጭምር ማሳሰባቸውን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡