“የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” የሚል የወጣቶች ንቅናቄ

ጳጉሜ 02/2013 (ዋልታ) “የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” በሚል መሪ ሃሳብ የአሸባሪውን ሕወሓት ሀገር የማፍረስ እቅድ ለማጋለጥ የወጣቶች ንቅናቄ ከመስከረም 3 እስከ 15 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ።

‘የኢትዮጵያ ዮዝ ኢንፓወርመንት’ ማኅበር እና ሀገር አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄ አስተባባሪ ዓለምአየሁ ሰይፉ፤ የወጣቶች ንቅናቄው በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመመከት መሆኑን ገልጿል።

“በኢትዮጵያ ላይ በተሳሳተ መልኩ የሚነዛው አሉባልታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት በንቅናቄው ይሰራል” ብሏል።

“የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ-መንግስት” ዓለም አቀፍ የንቅናቄ የአስተባባሪ ኮሚቴው ምክትል ጸኃፊ አክሊሉ ታደሰ በንቅናቄው ከ5 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ ብሏል።

የኢትዮጵያውያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ፣ የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማፍረስ ወረራ ማጋለጥ፣ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሸባሪው ህወሓት የፈጸመውን ግፍ ማሳየት፣ የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያዊን የተጠላ መሆኑን ማሳወቅ የንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች መሆናቸውን ገልጿል።

ኢዜአ እንደዘገበው አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ወረዳዎችና እና ከተሞች የፖስታ ማሰባሰቢያ ጣቢያ ዝግጅት መደረጉም ታውቋል።

ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጠቀሜታ ይኖረዋል የተባለው “የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ-መንግስት” የፖስታ መልዕክት ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዲደርስ ይሰራል ተብሏል።