የነጭ ሣር ብሄራዊ ፓርክን ወደ ቀደመ ይዞታው ለመመለስ ሕገ-ወጦችን መከላከል ይገባል – ቋሚ ኮሚቴ

 

የነጭ ሣር ብሄራዊ ፓርክን ወደ ቀደመ ይዞታው ለመመልስ የጋሞ ዞን አስተዳደር በሕገ-ወጦች ላይ ተገቢውን ሕግ የማስከበር ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የቡድኑ አስተባባሪ ወይዘሮ ቸርነት ኃይለማሪያም አሳሰቡ፡፡

አስተባባሪዋ ወይዘሮ ቸርነት ኃይለማሪያም ይህንን ያሳሰቡት የነጭ ሣር ብሄራዊ ፓርክ ያለበትን ይዞታ አስመልክቶ ቡድኑ ከጋሞ ዞን አስተዳደር አመራሮች ጋር በነበረው ውይይት ነው ተብሏል፡፡

ቡድኑ ከአመራሩ ጋር በነበረው ውይይት የፓርኩ መለያ የነበረው ነጩ ሣር በሕገ-ወጥ ግጦሽ እና ሰደድ እሣት ምክንያት እንደጠፋ አስተባባሪዋ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ፓርኩ በሰደድ እሣት፣ በሕገ-ወጥ አደንና በመሬት ወረራ ምክንያት ሕልውናው አደጋ ውስጥ እንደወደቀም ነው የገለጹት፡፡

በፓረኩ ውስጥ የሚገኘው የኩልፎ ወንዝ በከፍተኛ መጠን በመሙላቱ የፓርኩ 70 ሄክታር ደን በውሃ እንደተዋጠ እና ድልድዩ በደለል በመዋጡ ምክንያት ፓርኩን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች ለከፍተኛ ወጭ እየተዳረጉ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡

ፓርኩ ያለበትን ይዞታ ለመመልከት ቡድኑ ወደ ፓርኩ ያመራ ቢሆንም የኦነግ ሸኔ ቡድን ፓርኩ ውስጥ መመሸጉ እና በቡድኑ ላይ ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል በዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ስለተነገረው የኩልፎ ወንዝን ተሻግሮ ወደ ፓርኩ ምሥራቃዊ እና ምዕራባዊ ኦሮሚያ ክፍል መግባት አልቻለም ተብሏል፡፡

በፓርኩ ምዕራባዊና ምሥራቃዊ የኦሮሚያ ክፍል ሕገ-ወጥ ስራዎች ሲሰሩ ለመከላከል እና ሕገ-ወጦችን ወደ ሕግ ለማቅረብ የምዕራብ ጉጂ ዞን አመራሮች ተባባሪ አለመሆናቸውንም የመምሪያ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በፓርኩ ውስጥ የመሸገው ኦነግ ሸኔ የሰገንን እና አማሮ ብሄረሰቦችን እያተራመሰ እንደሚገኝም አቶ ሙናዬ አክለው ተናግረው፣ መንግስት ችግሩን እንዲፈታላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፓርኩን ይዞታ ለማየት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ 2009 እና በ2011 ዓ.ም. ወደ ፓርኩ መምጣታቸውን የገለጹት የፓርኩ ስራ አስኪያጂ አቶ ሽመላሽ ዘነበ የፓርኩን ችግር አዳምጠው ከመሄድ ውጭ በጊዜው ተነስቶላቸው ለነበረው ችግር መፍትሄ አለመስጠታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የፓርኩ ወሰን ባለመካለሉ ምክንያት በፓርኩ ምዕራባዊ ኦሮሚያ በኩል ፓርኩ የኦሮሚያ ነው ሚል የባለቤትነት ጥያቄ እየተነሳ እና ከፍተኛ ሕዝብ የማስፈር አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ ስለሆነ የፓርኩ ሕልውና ሳያከትምለት መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለችግሩ እልባት እንዲፈልግለት ቡድኑን መማጸናቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡