የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ገቡ

መሰከረም 23/2014 (ዋልታ) – የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሃሙዱ ቡሃሪ ነገ በሚካሄደው የመንግስት ምስረታ ስነ-ሥርዓት ላይ ለመታደም በአዲስ አበባ እንደሚገኙ የናይጄሪያ ጋርዲያን ዘገባ አመለከተ።
ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቅሷል።
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ሃላፊነት ሲመጡ ፕሬዝዳንት ቡሃሪ የመልካም ምኞት መግለጫ መላካቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ናይጄሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጿል።
ኢዜአ እንደዘገበው በኢትዮጵያ በሚካሄደው የመንግስት ምስረታ ስነ-ሥርዓት ላይ ለመታደም የተለያዩ እንግዶች እየገቡ ሲሆን፣ ትናንት አዲስ አበባ የገቡት የናይጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፍሬይ ኦኒዬማ ከእንግዶቹ መካከል ይገኙበታል።