የአማራ ሕዝብ የኅልውና አደጋውን በድል ማጠናቀቅና ልማቱን ማፋጠን እንደሚገባው ተገለፀ

ታኅሣሥ 17/2014 (ዋልታ) “የአማራ ሕዝብ በመደራጀት የኅልውና አደጋውን በድል ማጠናቀቅ እንዲሁም ልማቱን ማፋጠን ይገባዋል” ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።
በጎንደርና አካባቢው ስላለው ሰላም፣ ልማትና የመልሶ ማቋቋም ጉዳዮች ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ምክክር የተደረገበት ሲሆን የፌደሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሰፊ የመልማት እድል ያለው ጎንደር በዛው ልክ የፀጥታ ችግር እንዳለበት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተረባርቦና ተደራጅቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአሸባሪው ትሕነግ ዋነኛ ዓላማ አማራን በማንበርከክ ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበትም አስታውሰዋል፡፡
“የአማራ ሕዝብ በኅልውና ዘመቻው ያሳየውን አንድነት በልማት ሥራዎችም መድገም ይገባዋል” ሲሉም አክለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ሚኒስትሮችና ሌሎች በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳታ ሆነዋል፡፡
በደምሰው በነበሩ (ከጎንደር)