የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ የልዩ ሃይል ፖሊስ አባላትን አስመረቀ

ጥቅምት 16/2014 (ዋልታ) የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ለ9ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት አስመረቀ፡፡
በምርቃት መርሃ ግብሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡
ርዕስ መስተዳድሩ ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በንግግራቸው ነፃነትና ክብር ያለመስዋዕትነት አይገኝም ብለዋል፡፡
ጀግንነት በአውደ ግንባር የሚፈጠር ነው ያሉት ርዕስ መስተዳድሩ፣ ተመራቂዎች ለአርበኝነት እና ድል እንዲተጉ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኮሌጁ ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አንማው አለሜ ከመከላከያ እና ሌሎች ጸጥታ ሃይሎች ጋር በየአውደ ውጊያው ጠላትን ድባቅ እየመታ የሚገኘው የአማራ ልዩ ሃይልን የተቀላቀሉት ክንደ ነበልባሎቹ የአማራ ልዩ ሃይል አባላት አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው መመረቃቸውን ተናግረዋል።
ተመራቂዎች በአውደ ውጊያ ላይ ጀግንነት፣ ዓርበኝነትን እና ተዋጊነትን በተግባር እንዲያሳዩም አደራ ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በበኩላቸው ተመራቂ የልዩ ሃይል አባላት ህዝባዊ አደራቸውን በወታደራዊ ስነ ምግባር እንዲወጡ አሳስበዋል።