የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ወደ ኢትዮጵያ ሊጓዙ ነው

ነሃሴ 07/2013 (ዋልታ) – የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ለሦስተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሦስት የአካባቢው ሀገራት ሊጓዙ መሆኑ ተነገረ፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ልዩ መልዕክተኛው ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያና ጂቡቲ እንዲሁም ወደ ባሕረ ሰላጤው በማቅናት ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ይጎበኛሉ ተብሏል።
ልዩ መልዕክተኛው ጄፍሪ ፌልትማን ከመጪው እሁድ ነሐሴ ጀምሮ ለአስር ቀናት በሚያደርጉት ጉዞ ከሀገራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ካጅ ሱሉቫን የልዩ መልዕክተኛው ጉዞ ይፋ ከመሆኑ በፊት በትዊተር ገጻቸው ላይ ፌልትማን “በዚህ ወሳኝ ወቅት” ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓዙ በፕሬዝዳንቱ መጠየቃቸውን ገልጸው ነበር።
“ለወራት የተካሄደው ጦርነት በበለጠ ግጭት ሊሽር የማይችል ከፍ ያለ ስቃይንና መከፋፈልን በታላቋ ሀገር ላይ አስከትሏል” በማለት ሁሉም ወገኖች በአስቸኳይ ወደ ድርድር እንዲመጡ ጠይቀዋል ጃክ ሱሉቫን።
የልዩ መልዕክተኛው ጄፍሪ ፌልትማን ዋነኛ የጉዞ አላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት ጉዳይ መሆኑን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው አመላክተዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የልዩ መልዕክተኛውን ጉዞ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው “ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም ለማስፈንና መረጋጋትን እንዲሁም ብልጽግናን ለመደገፍ ያሉ ዕድሎችን” በተመለከተ ውይይት ይደረጋል ብሏል።
የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ያወጀ ቢሆንም አሸባሪው ቡድን ጥቃቱን ወደ አጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች በመስፋፋቱ መንግስት የመከላከያ ሰራዊትና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳውን የሽብር ቡድን እንዲደመሰሱ ትዝዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡