የአምራች ኢንደስትሪዎች የንቅናቄ መድረክ ተከፈተ

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የተዘጋጀው ንቅናቄ መድረክ በይፋ ተከፍቷል።
በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እና ሌሎች የፌዴራል መንግሥትና የከተማው ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ተሰፍሮ የማያልቅ ተፈጥሯዊ ሃብትን፤ በታደለችው ከመቶ ሚሊዮን በሚልቀው የህዝብ ቁጥሯ ውስጥ አብዛኛው በአምራች እድሜ ክልል ውስጥ በሚገኝባት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነን ተባብረን ከሰራን በአጭር ጊዜ ብልፅግና ላይ መድረስ እንችላለን ብለዋል።
“ብልፅግና ያለ አድካሚ ስራና ጥረት ከቶውንም ሊሳካ አይችልም” ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በሃገራችን ከተሞች ለስራ ፈላጊዎች የተለያዩ አማራጮችን ለማመቻቸት የከተሞችን የሥራ እድል ማጠናከር እና የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ድጋፍን በማከናወን ለነገ የምንለው ተግባር አይደለም ብለዋል።
ከንቲባዋ ለኢንደስትሪው የምናደርገውን ድጋፍ በመፈተሸ አዳዲስ አሰራሮችንም በመተግበር የተሻለ ውጤት እንደምናስመዘግብ እምነቴ ነው በማለት የከተማ አስተዳደሩ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊው ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፣ የሚሰሩ እጆችን ከስራ ጋር ለማገናኘት በከተማችን ከተያዘው እቅድ አንዱ ኢትዮጵያ ታምርት የሚለው ንቅናቄ አንዱ መሆኑን አንስተው በዚህም ከዘርፉ በአመት ከፍ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።
ከተለመደው መንፏቀቅ ለመውጣት የተለየ ንቅናቄ አስፈልጓል ፤ ለዚህም ሃገር ውስጥ ምርት መሻሻል እና የሥራ ባህል ማሳደግ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የዛሬው ንቅናቄ አሁን ላይ ካሉን 10 ሺሕ 500 አምራች ኢንዱስትሪዎችን ቁጥር ወደ 22 ሺሕ ለማሳደግም እንደሚረዳ ነው የጠቆሙት።
በተጨማሪም ያለ ኢንዱስትሪ ልማት ያደገ ሀገር አለመኖሩን ያነሱት ጃንጥራር አባይ “እኛም እንደ ሀገር ለመበልፀግ የተለያዩ ፖሊሲዎችን አሻሽለን ከኢንዱስትሪያሊስቶች ጋር ተቀራርበን መስራት አለብን” ማለታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።