የአረቡ አለም መሪዎች አገር መውደድን ከዐቢይ አሕመድ ተማሩ – ቱኒዚያዊ ጋዜጠኛ

ኅዳር 21/2014 (ዋልታ) የአረቡ አለም መሪዎች አገር መውደድን እና ለሃገር መሞትን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተማሩ ሲል ቱኒዚያዊው ጋዜጠኛ ሳሊህ አልአዝረቅ ገለጸ፡፡
በአረቡ ዓለም ታዋቂ የሆነው ጋዜጠኛ ሳሊህ በአል ሂዋር ቴሌቪዥን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተንቀሳቃሽ ምስል እያሳየ “በዚህ የቴሌቪዥን ስክሪን ላይ የምታዩት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነው ፤ ይህ ሰው ስልጣኑን ለምክትሉ በመስጠት የወታደር ዩኒፎርም ለብሶ አማፂዎችን ፊትለፊት እየተዋጋ ነው“ ብሏል፡፡
ጋዜጠኛ ሳሊህ ንግግሩን ሲቀጥልም “ምናልባት ይህ ክስተት ለኛ ለአረቦች አዲስ ሊሆን ይችላል፤ በኢትዮጵያውያን ግን ይህ ተግባር የተለመደ ነው፤ ጀግንነት የራሳቸው ነው“ ሲልም ተናግሯል፡፡
የትኛው የአረብ መንግስት ወይም የፓርላማ አባል ወይም ባለሀብት ነው ለአገሩ ሲል ስልጣኑን ጥሎ ሊዋጋ ጫካ የወረደው? ሲል ይጠይቅና “ማንም የለም!“ በማለት ሲመልስ ተደምጧል፡፡
ጋዜጠኛ ሳሊህ ለ50 ደቂቃዎች በዘለቀው የቴሌቪዥን መርኃግብሩ የአረቡ አለም መሪዎች እንዲያውም በተቃራኒው እንደሚነሱ በመግለጽ ክፉኛ ተችቷል፡፡
ለአብነትም የቱኒዚያ መንግስት ስልጣን ለመያዝ ብሎ ያንን ሁሉ ህዝብ ጨፈጨፈ፣ የግብፁ ፕሬዝዳንትም መፈንቅለ መንግስት ፈጽሞ እና በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ጨፍጭፎ ወደስልጣን መጣ፣ የየመኑ ፕሬዝዳንትም የአገሩ ህዝቦችና ወታደሮች ከአማፂዎች ጋር እየተዋጉ ባሉበት ሁኔታ እሱ ግን አገሩን ለቆ በሳኡዲ ቅንጡ ሆቴሎች መሽጎ እነሱ ታግለው እስኪያሸንፉ እየጠበቀ ነው ብሏል።
ዐቢይ አሕመድ ግን፣ ስልጣኑን ለምክትሉ በመስጠት አማፂዎችን እየተዋጋ ነው፤ ምናልባት በዚህ ውጊያ ላይ ሊሞት አሊያም ሊቆስል ይችላል፤ ይህ ሰው ግን አገሩን ምን ያህል እንደሚወዳት ብቻ ሳይሆን የአገር ፍቅር ከስልጣን በላይ መሆኑን ለመላው አለም አሳይቷል ሲልም አክሏል።
የምዕራባውያንን ተላላኪ ሥርዓት አገሬ ላይ ከማስፍን እዋጋለሁ ብሎ ለማንም የማይላላክ መንግስት መሆኑን አሳይቶናል ብሏል።
ጋዜጠኛው መርኃግብሩን ሲያጠቃልልም ማነው የዐቢይ አሕመድን መንገድ የሚከተል? ሲል ጠይቋል፡፡