የአርበኝነት መንፈስ የምንላበስበት ወቅት ላይ እንገኛለን- አቶ ተስፋዬ በልጂጌ

አቶ ተስፋዬ በልጂጌ

ነሐሴ 24/2013 (ዋልታ) – የአርበኝነት መንፈስ የምንላበስበት ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ ገለጹ፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የ2014 እቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እንያካሄደ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም አሁን ላይ ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ የጥፋት ሀይሎች እየተፈተነች በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ የአርበኝነት መንፈስ በመላበስ በጋራ የምንቆምበት ወቅት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን በታሪክ የውስጥና የውጭ ሀይሎች ሲፈታተኗት የመጀመሪያ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ነገር ግን ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የኖረች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

የውጭ ሀይሎች ከተላላኪያቸው አሸባሪው ትህነግ ጋር ኢትዮጵያን የማፍረስ እና የማዳከም ስትራቴጂ አንግበው እየተንቀሳቀሱ የሚገኝበት ወቅት በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ ቆመን ጠላቶቻችንን ድል የምናደርግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን በማለት ተናግረዋል።

ጦርነቱ የተከፈተብን በግንባር ብቻም ሳይሆን በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት እና በኢኮኖሚ አሻጥር ጭምር ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ በልጂጌ፣ ኢትዮጵያን ለማዳን የትም፤ መቼም፤ በምንም እዘምታለሁ የምንለውም ለዚሁ ነው ሲሉ አክለዋል።

አቶ ተስፋዬ በልጂጌ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተወክለው በመድረኩ ለተገኙ ባለሙያዎች ባስተላለፉት መልዕክትም ወሳኝ ናቸው ያሏቸውን አራት ነጥቦች አጋርተዋል።

በየተሰማሩበት የከፍተኛ ትምህርት ቦታ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን መስራት እንደሚጠበቅባቸው፣ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎች በመመከት በየአካባቢያቸው ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች እውነተኛ መረጃዎችን ብቻ እንዲያጋሩ፣ በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንደሚጠበቅባቸው እና በተደራጀና በተናበበ ሁኔታ ህዝብና ሀገርን በሚጠቅም ተግባር  መሰለፍ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

(በደረሰ አማረ)