የአርበኝነት ንቅናቄው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብ መሆን እንዳለበት ተገለጸ

ኅዳር 15/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ላይ ለተከፈተባት ጦርነት የሚያስፈልገው የአርበኝነት ንቅናቄ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች መሆን እንዳለበት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ቦንጋ ከተማ በተካሄደው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምስረታ በእንግድነት የተገኙት አስተባባሪው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች ኢትዮጵያ ላይ በቅንጅት የከፈቱትን ጦርነት የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ጦርነት ነው ብለውታል።

ይህ ጦርነት ኢትዮጵያ እንድትወድቅ የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቿ የውስጥ ተላላኪዎችን ቀጥረው በተቀናጀ መንገድ የከፈቱት እንደሆነም አንስተዋል።

ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለመታደግና የጠላቶቻቸውን ጥቃት ለመመከት የአርበኝነት ንቅናቄ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው ንቅናቄው ግን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን ተናግረዋል።

ዳግም ባርነት እና ቅኝ ግዛትን አንቀበልም የሚሉ መላው ጥቁር ሕዝቦች የኢትዮጵያን የአርበኝነት ንቅናቄ ተቀላቅለው በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ በጋራ እንዲሰለፉም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን የሚወድ፣ ባርነትን እና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን የሚጸየፍ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ግንባር እንዲዘምትና አገሩንም ቀና እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት መረጋገጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው በሚፈለጉበት ቦታ ሁሉ ለመሰለፍ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በሌላ ዜና ቢቂላ (ዶ/ር) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምስረታ የሕዝብ ጥያቄ በሕገ መንግስታዊና በሠላማዊ መንገድ እንደሚፈታ ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 11ኛው ክልል ሆኖ ትናንት በይፋ መመስረቱ ይታወቃል።

አሸባሪው ሕወሓት ስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት የክልልነት ጥያቄ የሚያነሱ ሕዝቦችን ሲያስር፣ ሲሰውር እና ሲገድል መቆየቱን አስታውሰዋል።

ነገር ግን ባለፉት ሶስት ዓመታት የዜጎችን ሠብዓዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሕገ-መንግስታዊ መብቶች በተግባር ለመመለስ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

የሕዝቦች ጥያቄዎችን በመመለስ አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል።

የሲዳማ ክልል ባለፈው ዓመት ያካሄደውን የክልል ምስረታ ለአብነት ጠቅሰው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው በሕዝበ ውሳኔ ክልል መመስረታቸውን ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምስረታ የማንኛውም ሕዝብ ጥያቄ በሕገ መንግስታዊና በሠላማዊ መንገድ እንደሚፈታ መልዕክት ያስተላለፈ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም ዴሞክራሲና ፌዴራሊዝም ከወረቀት ላይ ባለፈ በተግባር የተገለጠበት መሆኑን ዜጎች በተጨባጭ ምስክርነት እየሰጡበት ያለ ጉዳይ ነው ብለዋል።