የአርቲስት አለማየሁ እሸቴ አስከሬን ሽኝት በመስቀል አደባባይ

የአርቲስት አለማየሁ እሸቴ አስከሬን ሽኝት

ጳጉሜ 02/2013 (ዋልታ) – የአንጋፋው አርቲስት አለማየሁ እሸቴ አስከሬን ሽኝት በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው።

በሽኝት ስነ-ሥርዓቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የኪነ-ጥበብ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

አንጋፋው አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ባለፍነው ሐሙስ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ባደረበት የልብ ሕመም በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል።

“ወርቃማው” እየተባለ ለሚጠቀሰው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን ሥሙ በጉልህ የሚጠራው ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ ስርአተ-ቀብሩ በዛሬው እለት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።

ከ300 በላይ የሙዚቃ ሥራዎችን ያበረከተው ዓለማየሁ እሸቴ፣ “ጌሪ ኮፐር”፣ “ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ”፣ “ዓለማየሁ ቴክሱ፣ ነጭ ነው ፈረሱ” በሚል በአድናቂዎቹ ተወድሷል።

የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም አቀፍ መድረኮች በማቅረብም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተወዳጅነት እንዲያገኝ ያደረገ አንጋፋ ድምጻዊ ነበር።

ለመጀመርያ ጊዜ በ1955 ዓ.ም በፖሊስ ሠራዊት ኦኬስትራ ውስጥ በመቀጠር የሙዚቃ ‘ሀሁ’ን የጀመረው፤ አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ በወቅቱ በሚጫወታቸው የሙዚቃ ስራዎቹ ኤልቪስ ፕሪስሊ የሚል ቅፅል ተሰጥቶት ነበር።

“ተማር ልጄ” እና “አዲስ አበባ ቤቴ” በሚሉት የሙዚቃ ስራዎቹ ከፍተኛ ታዋቂነትንና ተወዳጅነትን ያተረፈው አንጋፋው ሙዚቀኛ አለማየሁ፤ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ከፍ ወዳለ ደረጃ ካደረሱት ድምፃዊያን መካከል አንዱ ነው። ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡