የአሸባሪውን ሕወሓት ቡድን ግብዓተ ቀብር ለመፈጸም በጋራ መቆም እንደሚገባ ተገለጸ

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) ከኢትዮጵያ ህዝብና ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን የአሸባሪውን ሕወሓት ቡድን ግብዓተ ቀብር ለመፈጸም በጋራ መነሳት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔን የሚያወግዝ እና ጀግናውን የአገር መከላከያ ሰራዊት የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ የዞኑ ነዋሪዎች አካሂደዋል፡፡
የዞን ዋና አስተዳዳሪ መሐመድ ጀማል እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለዘመናት የተወዘፈውን የህብረተሰቡ የዴሞክራሲ እጦት ጥያቄ ምላሽ መስጠት የተጀመረበት በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለመበታተን የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ የህልውና አደጋ የደቀኑበት ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡
አሸባሪዎቹ የሕወሓት ቡድንና ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያልተገባ ጋብቻ ፈጽመዋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ይህንን ለመመከት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ እኛ እያለን ሀገር አትፈርስም ይልቁንም ሽብርተኞቹ ለአንዴና ለመጨረሻ ጠራርጎ ግብዓተ ቀብራቸውን በመፈጸም የሀገሪቱን አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነስቷል ብለዋል።
ወጣቱ ወደ ግንባር በመዝመት፣ አቅም የሌለው ገንዘብ በመለገስ፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ሞራል በመስጠት፣ ጸሎት በማድረግ እንዲሁም ተደራጅቶ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ በመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ማህበረሰብ በአገሪቱ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት ከመንግስትና ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ድጋፉን በአገሪቱ የተቃጣው ጥቃት እስኪወገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።