የአሸባሪው ሕወሓት ኃይሎች የሰሩትን ወንጀልና ጥፋት ሌላው ላይ ማላከክ ባህላቸው አድርገውታል – ፖለቲከኛ አንዳርጋቸው ጽጌ

ፖለቲከኛ አንዳርጋቸው ጽጌ

ኅዳር 9/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያውያን የተፈጸመባቸውን ግፍና ዘረፋ ትተው በይቅርታ ያለፋቸው ወንጀለኞች በተቃራኒው የኢትዮጵያን መንግሥትና ሕዝብ ለመክሰስና ካሳ ለመጠየቅ ማሰባቸው የሚያሳፍር፣ ወንጀልና ጥፋት መሥራት ባህላቸው ማድረጋቸውን የሚመሰክር መሆኑን ፖለቲከኛ አንዳርጋቸው ጽጌ ገለጹ።

የወያኔ ሽብር ቡድን እንደ ድርጅት ከተመሰረተ ጀምሮ በታሪኩ የራሱን ወንጀል፣ ጥፋትና ስህተት አምኖ የማያውቅ፣ የሰራውን ወንጀል ሌላው ላይ ማላከክን ባህሉ ያደረገ መሆኑንም ገለጸዋል።

‹‹የዘረፋችሁትን መልሱ፣ ለፈጸማችሁት ወንጀል ተጠየቁ›› መባል የሚገባቸው እነርሱ ሆነው፤ ሕዝቡ የገደሉትን ወልደን፣ የዘረፉትንም ሰርተን እንተካለን ብሎ በይቅርታ ያለፋቸው ወንጀለኞች በተቃራኒው አይን አውጥተው የኢትዮጵያን መንግሥትና ሕዝብ ለመክሰስና ካሳ ለመጠየቅ ማሰብ በራሱ የሚያሳፍር ድርጊት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ያንን ሁሉ ግፍ፣ ዘረፋና የበቀል ወንጀል የፈጸሙበትን ትቶ አገርን በሰላም ለማሻገር ከጦርነት፣ ከበቀል አዙሪት ለመውጣት በማሰብ፤ የገደሉትንም ይቅር እንበላቸው ማለቱንም አስታውሰዋል።

እንደ ኢፕድ ዘገባ ከወያኔና ተባባሪዎቻቸው ጋራ የእርቅና የድርድር ቀና መንፈስ ብናሳያቸው ከሰይጣናዊ አመለካከታቸው ይመለሳሉ የሚል አስተሳሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናትና ዜጋው ሙሉ ለሙሉ በማስወገድ ወንጀለኞቹ እንዲጠየቁ ሥራውን መጀመር ይኖርበታል ብለዋል።