የአሸባሪዎቹን አገር የማፍረስ ሴራ ለመቀልበስ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ኅዳር 16/2014 (ዋልታ) አገር የማፍረስ ዓላማን ያነገቡ አሸባሪዎች ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ በጠንካራ ትብብር መስራት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው “ዲፕሎማሲያችንን በአዲስ ምዕራፍ ለላቀ ለውጥ” በሚል መሪ ቃል የሚሲዮን መሪዎችና የዋናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ዓመታዊ ስብሰባ ሲጀመር ነው ይህን የገለጹት።

አገርን ለማፍረስ እና ለማተራመስ እየተደረገ ያለውን የአሸባሪዎችና የተባባሪዎቻቸውን ተልዕኮ ለማምከን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅ አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።

ተቋማዊ ለውጥና አገልግሎት አሰጣጥ አፈጻጸምን ለማሳደግ ከዚህ በፊት በተቋሙ ሥራ ላይ እንዲውሉ የተደረጉና ወቅታዊ ያልሆኑ መመሪያዎችን በማሻሻል፣ የአደረጃጀት ክፍተቶችን በመለየት፣ ተቋማዊ ለውጥ ከታህሳስ 2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን አብራርተዋል።

በሚኒስቴሩ ጊዜ ተወስዶ ሲሰራበት የቆየው የለውጥ ሥራ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገው የለውጥ ሥራ አንዱ አካል መሆኑን እና አሁናዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ማከናወን እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረጸ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በዓመታዊ ስብሰባው የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ፣ በተቋሙ እየተደረገ ያለው የለውጥ ሥራ ላይ መረጃ መለዋወጥ እና መወያየት እንዲሁም የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ መወያያት ተጠቃሽ የውይይት አጀንዳዎች ሲሆኑ በዛሬው ውሎም 2013 ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ወይይት እንደሚደረግበት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡