የአውሮፓ ህብረት በትግራይ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ በማጣራት ሂደቱ ጣልቃ መግባት ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር


ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) –
የአውሮፓ ህብረት በትግራይ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ እየተካሄደ ባለው የማጣራት ሂደት ጣልቃ መግባት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የአውሮፓ ህብረት በትግራይ የሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ያሳለፈው ውሳኔ እንዳዛዘነው አመልክቷል።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል በተካሔደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ወቅት ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ከተወጣጡ አካላት ጋር መርማሪ ቡድን ለማሰማራት መንግስት መስማማቱ ተመልክቷል፡፡
የጋራ ቡድኑ በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ምርመራውን የጀመረ ሲሆን ነሐሴ 2021 ሥራውን ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም የወታደራዊ የፍትህ ስርዓትን፣ የክልል ህግ አስከባሪ ባለሥልጣናትን፣ የፌዴራል መርማሪዎችን እና ዓቃቤ ሕግን በማቀናጀት ምርመራዎች በስፋት እየተደረጉ መሆኑን አውስቷል።
ህብረቱ ውሳኔውን ከማሳለፉ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት የውሳኔ ሃሳቡን በተመለከተ ያቀረበው አቤቱታ ከግምት ውስጥ እንዳልገባ ገልጿል።
ውሳኔው እጅግ የፈጠነና የተቀናጀ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁኔታ ላይ የሚካሄደው የምርመራ ሂደቱ ላይ ጣልቃ መግባት መሆኑን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
መንግስት ጉዳዩ እንዲጣራ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ ባለበት ወቅት ውሳኔው መተላለፉ ተገቢ እንዳልሆነ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ይህ ሁሉ ጥረት እየተደረገ ውሳኔው መተላለፉ የሞራልም ሆነ የህግ መሰረት እንደሌለው ገልጾ፤ “ውሳኔው የፖለቲካ ፍላጎት እንዳለበት ተንጸባርቋል” ብሏል።