የአውሮፓ ህብረት የ4.4 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ

 

የአውሮፓ ህብረት ለቦማ-ጋምቤላ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ፕሮጀክት 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ፡፡

ህብረቱ የምስራቅ አፍሪካ በይን መንግስታት /ኢጋድ/ በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለመደገፍ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ስምምነቱን የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና በጅቡቲ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ አምባሳደር ኤይዳን ኦሃራ ፈርመዋል፡፡

ከስምምነቱ በኋላ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ÷ በኢጋድና በህብረቱ መካከል ያለው የረዥም ጊዜ ግንኙነት እየጠነከረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው ስምምነቱ በህብረቱና በኢጋድ የጋራ ተነሳሽነት የተደረሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ መልካም ነገሮችን ለማስቀጠልና የተጋረጡ ቀጠናዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ይረዳልም ነው ያሉት።

አምባሳደሩ በበኩላቸው ኢጋድ በድንበር ተሻጋሪ የአካባቢ ጥበቃ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

እንዲሁም በትግበራው ወቅት የአካባቢውን ማህበረሰብ መሳተፍ እንዳለበትም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ቦማ-ጋምቤላ መልክዓ ምድር በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ ድንበር የሚገኝ ሲሆን የተለያዩ የዱር እንስሳት እንዲሁም ብርቅዬና የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ዝርያዎችን እንደያዘ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡