የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪካ ሕብረት ስር የተጀመረውን የሰላም ሂደት እንደሚደግፍ አስታወቀ

መስከረም 4/2014 (ዋልታ) የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪካ ሕብረት ስር የተጀመረውን የሰላም ሂደት እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሪታ ላራንጂነሃ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ወቅትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
አክለውም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ስለተከሰተው ግጭት እና መንግስት ችግሩን በሰላም ለመፍታት የተጓዘበትን ርቀት አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ሕብረት ስር ለሚደረገው የሰላም ውይይት ዝግጁ እና ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመው የአውሮፓ ሕብረትም ይህን ሂደት እንደሚደግፍ ያላቸውን እምነት ገልጸውላቸዋል፡፡
ዳይሬክተሯ በበኩላቸው የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር እንደሚፈልግ አብራርተዋል፡፡
አያይዘውም በአፍሪካ ሕብረት ስር ለሚደረገው የሰላም ሂደት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ የአውሮፓ ሕብረት በማንኛውም ጊዜ ለሰላም የሚደረግን ጥረት ይደግፋል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
በነስረዲን ኑሩ