የአውሮፓ ኅብረት የቀውስ አስተዳደር ኃላፊው በሶማሌና በትግራይ ክልል ጉብኝት አደረጉ

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) የአውሮፓ ኅብረት የቀውስ አስተዳደር ኃላፊ ኮሚሽነር ጃኒዝ ሌነርሲስ በሶማሌና በትግራይ ክልል ጉብኝት እንዳደረጉ አስታወቁ።

ኮሚሽነር ጃኒዝ ሌነርሲስ በሶማሌ ክልል በታሪክ ከፍተኛ የተባለው ድርቅ ያደረሰውን ጉዳት ጎዴ አካባቢ በመገኘት እንደጎበኙ ተናግረዋል፡፡

የተከሰተውን የምግብ እጥረት ለመፍታት የሰብዓዊ አቅርቦት በማድረስ በኩል ከክልሉ የሥራ  ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

የዕለት ደራሽ የሰብዓዊ አቅርቦቱ ብቻ ዘላቂ መፍትሔ ስለማይሆን በዘላቂነት ችግሩን መቅረፍ የሚያስችል መፍትሔ ላይ መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሚልከው የሰብዓዊ አቅርቦት እየተሻሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከትሕነግ ኃላፊዎች ጋር እንደመከሩ ገልጸው የገንዘብና የነዳጅ አቅርቦቱ መሻሻል እንዳለበት በመቀሌ ጉብኝታቸው እንደተመለከቱም ነው የተናገሩት።

ሁለቱን አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ እና ግጭቱ እንዲቆም በአፍሪካ ኅብረት በኩል የሚደረገውን የማደራደር ተግባርም የአውሮፓ ኅብረት እንደሚደግፍ አስታውቀዋል፡፡

በምንይሉ ደስይበለው