የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ

ነሀሴ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት በድሬዳዋ ከተማ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የክልል ፕሬዝዳንቶችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች፣የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የክልልና የከተማ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።

በስብሰባው  ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በራስ አቅም ድጋፍን ለማሟላት እስከ አሁን የደረሱበት ደረጃ  እና  ወቅታዊ የሆኑ ዘርፈ ብዙ አደጋዎች ክስተትና የሰብዓዊ ድጋፍ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቧል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ም/ቤት ሴክሬታሪያት አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም (ዶ/ር) ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የአገራዊ ደህንነት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው የክብር፣ የነፃነትና የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ በትኩረት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ  7 ዐበይት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።

  1. ከተፈጥሮ አደጋ ውጪ ያሉ ተፈናቃይ ዜጎችን ወደ ነበሩበት በመመለስ፥ ለምርታማነት እና ማቋቋሚያ በሚሆን የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መስራት።
  2. የተረጂዎችን እና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን የተጣራ መረጃ በመያዝ፥ የግል ማህደራቸውን በጥንቃቄ በመለየት አደራጅቶ ማስቀመጥ።
  3. ሀብትን በማሰባሰብ ረገድ ጥሩ አፈፃፀም ካሳዩ ክልሎች ተምክሮ በመቅሰም ተቀራራቢ የሆነ አፈፃፀም ላይ ለመድረስ መስራት።
  4. ቅፅበታዊ አደጋዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ ቅንጅታዊ ንቃተ ህሊና ይዞ መዘጋጀት እና የመሬት አጠቃቀምን በህግ ማዕቀፍ ማስተሳሰር፥ እንዲሁም በዝናብ ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን መለየት።
  5. በተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች ዘላቂ የሆነ መፍትሄ በእቅድ ውስጥ በማስገባት፥ የአደጋውን ቀጥተኛ ተጎጂዎች በማዕቀፍ ውስጥ ማካተት።
  6. የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ እና እርስ በእርስ የወንድማማችነት ባህልን ማጠናከር፤ እንዲሁም ክልሎች የያዙትን የመተሳሰብ እሴት አስቀጥለው በመጓዝ አብሮነታቸውን ማጠናከር።
  7. እቅዶችን በጊዜውና በወቅቱ በማጠናቀቅ የተጓተቱ እና የተንጠለጠሉ ስራዎችን መቅረፍ እንዲሁም በቀጣይ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ በጠራ እቅድ ማከናወን የሚሉ መሆናቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።