የአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት አባቶች በጉለሌ እዕዋት ማዕከል ችግኝ ተከሉ

ሰኔ 23/2013 (ዋልታ) – ከአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች በጉለሌ እዕዋት ማዕከል ችግኝ ተከሉ።

“በአብሮነት እሴት አዲስ አበባን አረንጓዴ እናልብሳት” በሚል በጉለሌ እፅዋት ማዕከል በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐግብር የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ዘርፈሽዋል ንጉሴ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ ከአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሁሉም ቤተ እምነቶች ከተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ችግኝ ተክለዋል፡፡

የሀይማኖት ተቋማት ምዕመናን በማስተባበር ለችግኝ መትከያ በተዘጋጀላቸው ሰፍራ እና በየእምነት ተቋሞቻቸው ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ለመጪው ትውልድ ልምላሜን ለማውረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ  ጥራቱ በየነ ገልጸዋል።

እምነትን ከማራመድ ውጪ በልማት በተለይ በማህበራዊ አገልግሎት እና በአካባቢን ልማት እና በሌሎች ተግባራት እያበረከቱት ያለውን ተሳትፎ በይበልጥ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

ፈጣሪ ምድርን ሲፈጥር አረንጓዴ አድርጎ ፈጥሯል፤ ሰውም አካባቢውን በመጠበቅ ለኑሮ የተመቸ እንድትሆን እና ወደ ቀድሞ አረንጓዴያማነት ለመመለስ በቤተ እምነቶች አካባቢ ችግኞችን በመትከል እና የተተከሉትን መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ የሀይማኖት አባቶች መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ምድረን አረንጓዴ ስናለብስ በህዝብ መካከል መስተጋብርን እና መተሳሰብን እንፈጥራለን ያሉት የሀይማኖት አባቶች ቤተ እምነቶች ሰፊውን ድርሻ በመውሰድ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል።

በዘንድሮው የክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ከ7.5 ሚሊየን በላይ ለምግብነት እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ችግኞችን የመትከል ስራ የተጀመረ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነትም ከ1 ሚሊየን በላይ ችግኞችን የመትከል ስራ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።