የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሲዳማ ክልል የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

 

ለሲዳማ ክልል የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ

የካቲት 15/2013 (ዋልታ) – የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ምስረታ ክብረ በዓል ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ንግግር አድረገዋል፡፡

በንግግራቸዉም “ዋና ከተማቹ አዲስ አበባ ደስታቹ ደስታዬ ነው ብላ አብሮነትን እና ፍቅሯን ለመግለጽ ያደረገችው የገንዘብ ስጦታው የሲዳማ ክልል ሆኖ በመመሰረቱ የእንኳን ደስ አላችሁ ነው በማለት አስረክበዋል።

ህዝቦች ነጻነታቸው ሲረጋገጥ፣ ጥያቄያቸው ሲመለስ፣ እራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩ ኢትዮጵያ የምትፈርስ የሚመስላቸው አካላት የሲዳማ ክልል ሆና ስትመሰረት መላው ኢትዮጵያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ሰብስባ የኢትዮጵያዊነት ድምቀት፣ ዉበት በአንድ ላይ የደስታው ተካፋይ በማድረግ ኢትዮጵያ አንድ መሆኗን በተግባር አሳይቶናል ብለዋል።

አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያዊያን ከተማ ናት ያሉት ወ/ሮ አዳነች የሲዳማ ህዝቦች ትውፊታዊ ባህልን በከተማዋ የባህል ማዕከል እንደሚካተት ተናግረዋል።

በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ ከሲዳማ ክልል ጋር ያለውን ግንኙነት በይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና የሀዋሳ ከተማ የአዲስ አበባ እህት ከተማ በመሆን አብረን እንበለጽጋለን በማለት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች ሲዳማን ለመደገፍ እና ለማቋቋም ላደረጉት ድጋፍ እና ላሳዩት አጋርነት በክልሉ ህዝቦች ስም አመስግነዋል።

ዘገባዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሰክሪታሪያት ነዉ።