የአዲስ አበባ ፖሊስ ለቦክሰኛ ም/ሳጅን ቤተልሔም ገዛኸኝ የ150 ሺሕ ብር ድጋፍ አደረገ

ሰኔ 14/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ሀገሯን ወክላ ስትጫወት ጉዳት የደረሰባት ቦክሰኛ ምክትል ሳጅን ቤተልሔም ገዛኸኝ የህክምና ወጪን ለማገዝ የ150 ሺሕ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ባደረጉት ንግግር የተቋሙ የቦክስ ቡድን አባላት ከተቋሙ ባሻገር የሀገርን ስም የሚያስጠራ ውጤታማ ድል የሚያስመዘግቡ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል ብለዋል፡፡

ምክትል ሳጅን ቤተልሔም ገዛኸኝ ወደ መልካም ጤንነቷ ተመልሳ ህልሟን እንድታሳካ የአዲስ አበባ ፖሊስ እስከ መጨረሻው ከጎኗ እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

ምክትል ሳጅን ቤተልሄም በቦክስ ስፖርት ውጤታማ ሆና ሀገርን እስከ መወከል ያደረሳትን የአዲስ አበባ ፖሊስን በማመስገን በተደረገላት ድጋፍ መደሰቷን እንደገለጸች የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

ከቀናት በፊት ከአዲስ ዋልታ ጋር ቆይታ ያደረገችው ምክትል ሳጅን ቤተልሔም ሁለቱም ትከሻዎቿ ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልጋቸው እንደተነገራትና ለህክምናው አስከ 500 ሺሕ ብር እንደሚስፈልግ መናገሯ ይታወሳል፡፡

ምክትል ሳጅን ቤተልሔም ገዛኸኝ በጋና አክራ በተካሄደው 13ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ላይ ሀገሯን ወክላ በመሳተፍና የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ታሪካዊ ድል ያስመዘገበች ቦክሰኛ ናት።

የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የ52 ኪሎ ግራም ተወዳዳሪ የሆነችው ምክትል ሳጅን ቤተልሔም በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የማንዴላ መታሰቢያ ዋንጫ የቦክስ ውድድር ላይ ባጋጠማት የቀኝ ትከሻ ውልቃት ምክንያት ውድድሩን መቀጠል ባለመቻሏ ሁለተኛ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ለሀገሯ የብር ሜዳሊያ ማስመዝገቧም ይታወቃል።