የአዳማ ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት አዳማ ፖርታል የመጀመሪያ ዙር ትግበራ ይፋ ሆነ

የአዳማ ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት

ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – በአዳማ ዩኒቨርሲቲ እና በአዳማ ከተማ አስተዳደር የተጀመረ ከተማዋን በቴክኖሎጂ የሚያስተሳስረው የአዳማ ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት አዳማ ፖርታል የመጀመሪያ ዙር ትግበራ ይፋ ሆነ፡፡

በመርኃግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሀይሉ ጀልዴ አዳማ ከተማ በመልካም አስተዳደር፣ በንግዱ ዘርፍ እንዲሁም በኢኮኖሚው ፍሰት ፈጣን እና ዘመናዊ አሰራርን ከተከተለች እድገቷ ከታሰበለት ከፍታ ይደርሳል ብለዋል፡፡ ይህንንም ከግብ ለማድረስ የስማርት አዳማ ፕሮጀክት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

የአዳማ ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት በሞባይል መተግበሪያዎች ውስጥ የከተማ ኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የከተማዋ የመሬት አስተዳደር እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ የመንገዶች ፍሰት መካተታቸው ተጠቁሟል።

በአዳማ ከተማ አስተዳደር እና በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ተሰናድቶ የመጀመሪያው ዙር ይፋ የተደረገበት የስማርት አዳማ ፕሮጀክት የከተማዋ ነዋሪዎቸ ዘመናዊ እና ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ሲሆን፣ የዚህ መታወቂያ ባለቤቶች ለተለያዩ የባንክ አገልግሎቶች ምቹ ከመሆናቸው ባለፈ ወንጀልን ለመከላከል ፋይዳቸው የጎላ ነው ተብሏል።

የፖርትሬት አዳማ የመጀመሪያ ምዕራፍ የምረቃ ስነሥርዓት ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የከተማ ክላስተር አስተባባሪ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ተገኝተዋል።

(በቁምነገር አህመድ)