የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቀጣይ ወደ ትግራይ ክልል በመሄድ ህዝቡን እንደሚያወያይ ገለጸ

ጥቅምት 27/2015 (ዋልታ) በቀጣይ ተግባራችን የሚሆነው ወደ ትግራይ ክልል ሄደን ሕዝቡን እስከታች ድረስ ማወያየት ነው ሲሉ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ መስፍን አርአያ (ፕ/ር) አስታወቁ።
ሰብሳቢው እንደገለጹት፤ መላው ኢትዮጵያውያን የተሳካ የምክክር ሂደት እንዲያከናውኑ የትግራይ ሕዝብ ተሳታፊነት አስፈላጊ ነው።
የፌዴራል መንግስትና ሕወሓት ያደረጉት የሠላም ስምምነት እኛም ቀድመን ስንፈልገው የነበረው ጉዳይ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አገራዊ ምክክሩን በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ወደፊት ኮሚሽኑ በክልሉ ከሚገኘው ሕዝብ ጋር አስፈላጊውን ውይይት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።
የምክክር ኮሚሽኑን ቀጣይ ስራዎች የተሳለጠ ለማድረግ በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ የአስተዳደር አካላትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው።
በትግራይ የሚገኘው ሕዝብም የእኛው ሕዝብ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በአገራዊ የምክክር ሂደቱ ውስጥ ሕዝቡም ተሳታፊ እንዲሆንና ሃሳቡን መቀበል ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።