የአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በሕዝብ እንደሚመረጡ ተመላከተ

እፀገነት መንግስቱ

ታኅሣሥ 21/2014 (ዋልታ) የአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በሕዝብ እንደሚመረጡና ሹመታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚጸድቅ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ  በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የኮሚሽነሮች ጥቆማ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያሳትፍ ሲሆን ከተጠቆሙት 14 እጩዎች መካከል 11 ተመልምለው በአፈ ጉባኤው አቅራቢነት በምክር ቤቱ የሚሾሙበት አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።

ኮሚሽነሮቹ በምክር ቤቱ ከተሰየሙበት እለት ጀምሮ ለ3 ዓመታት የሚቆይ የስራ ጊዜ እንደሚኖራቸው ተጠቁሞ እንደ አስፈላጊነቱ ቆይታቸው ሊራዘም እንደሚችልም ተገልጿል።

በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ስለ ድርድር የሚገልጽ ምንም አይነት ይዘት አለመካተቱን ሰብሳቢዋ  ተናግረዋል።

የአዋጁ ዋና ዓላማ እስካሁን መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውና የኢትዮጵያን ኅልውና የሚፈታተኑ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያካተተ ውይይት በማድረግ ችግሮችን መፍታት እንደሆነ አመላክተዋል።

የሚቋቋመው ኮሚሽን ከምክክር መድረኮቹ የሚያገኘውን ምክረ ሀሳብ በመቀመር ተግባራዊ እንዲደረጉ እንደሚሰራ አንስተው ምክር ቤቱን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ወስደው እንደሚያስፈጽሙና ለስኬታማነቱም ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት እንደሚዘረጋ ሰብሳቢዋ መናገራቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ባካሄደው 2ኛ ልዩ ስብሰባው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁ ይታወቃል።