የአፋር ሕዝብ ሀገር ለማፍረስ በሚቅበዘበዘው ሕወሓት ላይ በሚመዘገበው ድል አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ ቀረበ

ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

ጥቅምት 23/2014 (ዋልታ) የአፋር ሕዝብ ሀገር ለማፍረስ የሚቅበዘበዘውን ሽብርተኛው ሕወሓት በመቅበር በሚመዘገበው ድል የአፋር ክልል ህዝብ አሻራውን እንያሳርፍ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ እንዳሳሰቡት የክልሉ ሕዝብ ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና ለመበተን የሚንቀሳቀሰውን ወራሪ ቡድን መግታት ይጠበቅበታል።

አሸባሪው ቡድነ በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎችን ለመግባት ቢሞክርም አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ በወረራ ከያዛቸዉ አካባቢዎች መባረሩን ገልጸዋል።

ቡድኑ በወረራ ይዟቸዉ በነበሩ አካባቢዎች መሠረተ ልማቶች በማዉደም ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ንጹሃንን በግፍ መጨፍጨፉን አስታውሰዋል።

ይህንን የቡድኑን ጸያፍና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ታሪክ በነውርነቱ የሚያስታውሰው ጥቁር ጠባሳ መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ ከስህተቱ የማይማር እብሪተኛ የጥፋት ስብስብ መሆኑን ጠቅሰው ስብስቡ ተላላኪዎቹን በማሰባሰብ አሁንም በበራህሌ፣ መጋሌና ጭፍራ ወረዳዎች ወረራ ለማድረግ እየሞከረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የሽብር ቡድኑ አላማ በፌዴራሊዝምና ብሄር ብሄረሰቦች ስም የሞግዚት አስተዳደሮችን መስርቶ ‘ለታላቋ ትግራይ ምስረታ’ ቅዠቱ ገባሮችን መፍጠር እንደሆነ አንስተዋል።

በመሆኑም የህብረተሰቡ ምርጫ አንድም የአሸባሪውን ህወሓት የቅኝግዛት አስተዳደር አሜን ብሎ ተቀብሎ ሃብቱንና ጊዜዉን ለዘራፊ ቡድኑ እየገበረ ማደር፤ አሊያም ከደምና አጥንቱ ከፍሎ ማናቸዉንንም መስዋእትነት በመክፈል ሀገራዊና ህዝባዊ ነጻነቱን፣ ክብሩንና ሀገራዊ ሉአላዊነቱ በማያወለዳ ሁኔታ በማረጋገጥ የአባቶቹን ታሪክ መድገም እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ የጠላቶቹን አላማና ሴራ በአግባቡ ተገንዝቦ ነጻነቱንና ክብሩን በደሙና አጥንቱ ለማረጋገጥ አጥብቆ በመፋለም የሽብር ቡድኑ የጥፋት አላማ በፍጹም ሊሆን የማይችል ቅዠት መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ ግድ የሚልበት ወቅት መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ መንግስትም የተከፈተውን ወረራ ለመቀልበስ የተጣለበትን ህዝባዊና ታሪካዊ አደራ በየደረጃዉ የሚገኙ አመራሮች ተቀዳሚ አጀንዳ አድርገዉ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህ የሀገርና የህዝብ ጠላት የሆነዉን የሽብር ቡድን ተገቢዉንና ተመጣጣኝ አጸፋ ለመስጠት ጉዳዩን የክልሉ መንግሰትና ህዝብ ተቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ መንቀሳቀስን ይጠይቃል።

በመሆኑም መከላከያ ሰራዊቱ ባለዉ ውስን ሃይል ሁሉንም ግንባር መሸፈን ሁሉም ቦታዎች መድረስ ስለማይችል ህዝቡ ክፍተቶችን ከመሙላት አልፎ እንደከዚህ ቀደሙ ህዝቡ ዋነኛ ተፋላሚ በመሆን አሻራውን እንዲያሳርፍ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ሁሉም የክልሉ ነዋሪ ያለዉ ማናቸዉም የነፍስ ወከፍ መሣሪያና ትጥቅ እንዲሁም ተያያዥ ግብዓቶች በመጠቀም ከልዩ ሃይሉና መከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመሠለፍ ክልላቸዉንና ህዝባቸዉን ከተደቀነበት አደጋ እንዲታደጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።