የአፋር ክልል ህዝብ በሰመራ ከተማ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ሰልፍ እያካሄደ ነው

የአፋር ክልልየድጋፍ ሰልፍ

ሐምሌ 18/2013 (ዋልታ) – የአፋር ክልል ህዝብ በሰመራ ከተማ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ሰልፍ እያካሄደ ይገኛል።

የአፋር ህዝብን ሲገድልና ሲያፈናቅል የኖረው አሸባሪው የህወሀት ቡድን ከአፋር ህዝብ ጋር ጠብ የለኝም በማለት የሀሰት ፕሮፖጋንዳውን እየነዛ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ሰልፈኞቹ ህዝባችን በእንዲህ አይነቱ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚሸወድ የመሰለው ጁንታ ነገም ሌላ የማደናገሪያ ወሬ መንዛቱ አይቀሬ በመሆኑ አሸባሪውን ከስሩ እንነቅለዋለን ብለዋል።

የህወሀት ቡድን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጠላት መሆኑን ከአፋር ህዝብ በላይ ምስክር የለም ሲሉም ሰልፈኞቹ ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን እና የትግራይ ህዝብ በፍፁም የተለያዩ ናቸው ያሉት የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች፣ ጁንታው በሉዓላዊነታችን ላይ ጥቃት በመፈፀሙ አንታገሰውም ብለዋል።

በሉዓላዊነታችን ላይ ተደራድረን አናውቅም፤ ዛሬም ወደፊትም አንደራደርም፤ አሸባሪን ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጥቃት በመፈፀሙ እናጠፋዋለን አንታገሰውም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት አሸባሪውን ለማጥፋት በሚወስደው እርምጃ የአፋር ህዝብ ደጀንነቱን ያስመሰክራል ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ህወሓት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ድርጅት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

(በደረሰ አማረ)