የአፍሪካን የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎትና ትንበያን በአፍሪካውያን አቅም ማዘመን እንደሚገባ ተጠቆመ

ሚያዚያ 13/2014 (ዋልታ) የአፍሪካን የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አሰጣጥና ትንበያን በአፍሪካውያን አቅም ማዘመን እንደሚገባ በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በዓለም የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጽህፈት ቤት፤ የአፍሪካን የሚቲዮሮሎጂ አልግሎት አሰጣጥና ትንበያ ለማዘመንና ለዘርፉ ተጠቃሚዎች ወቅታዊ መረጃ ለመስጠት የሚያስችል የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ትናንት ተጀምሯል፡፡

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2019 እስከ 2021 ድረስ፤ ዓለም መጥፎ የተባለውን የአየር ንብረት ለውጥ ያስተናገደች ሲሆን፤ በዓለም ላይ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ምክንያት ከአራት ቢሊዮን በላይ ህዝብ ለንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት እንደተዳረገም ይገለጻል፡፡

ከግማሽ በላይ የሆነው የዓለም ህዝብ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምክንያት በጎርፍ፣ በድርቅና መሰል ተፈጥሯዊ አደጋዎች እየተፈተነ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ ፈጠነ ተሾመ እንዳሉት፤ አፍሪካውያን በድርቅና ጎርፍ አደጋዎች ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገዱ ነው፡፡

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በአህጉሪቱ የሚቲዎሮሎጂ መሰረተ ልማቶችን ማጠናከር፣ ዘመናዊ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን መዘርጋትና የትንበያ አቅምን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባም ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለአቬዬሽንና ለጤና ዘርፎች አገልግሎት መስጠትና ተከታታይ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ አቅም መገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አሞስ ማካራው (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በቅርቡ የተከሰተው ድርቅ፣ በምስራቅ አፍሪካ የሚከሰተው ተደጋጋሚ ጎርፍና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች የታዳጊ ሀገራት ፈተና ሆነው ቀጥለዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከዚህ ችግር ለመውጣት አፍሪካውያን የራሳቸውን አቅም ተጠቅመው የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የራሷን አቅም በመጠቀም ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጂን እውን አድርጋ ለሌሎች አፍሪካውያን ሞዴል መሆኗን አሳይታለች ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡

የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጽህፈት ቤትን አደረጃጀት ለማዘመን 110 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገንዘብ መመደቡን ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ የዓለም ሚቲዮሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ጽህፈት ቤትም መቀመጫ ከሆነች ከሁለት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች፡፡