የአፍሪካ መንግሥታት የህፃናትን ጥቃት ለማስቆም የሚያደርጉትን ጥረት ሊያጠናክሩ ይገባል ተባለ

ግንቦት 3/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ መንግሥታት በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ።

የአፍሪካ ሀገራት ህፃናትን ከጥቃት ለመከላከል ያስችላሉ በተባሉ ፖሊሲዎች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።

እየተስፋፋ የመጣውን የህፃናት ጥቃት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ዙሪያ ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት መሪዎች በአዲስ አበባ ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።

የአፍሪካ ህፃናትና ወጣቶች መጠነ ሰፊ የሆነ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ፆታዊ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው የተባለ ሲሆን የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ፅንፈኝነት እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥቃቱ እንዲባባስ አድርጎታል ተብሏል።

ይህንንም በመገንዘብ በመላው የአፍሪካ አኅጉር ያሉ ፈር ቀዳጅና ተነሳሽነት ያላቸው ሀገራት በህፃናት ላይ በሚደርሰው ጥቃት ዙሪያ አሰራራቸውን ለማደስ፣ አፍሪካ በቀል የሆነ መፍትሄ ለማግኘት እንዲሁም እርስ በእርስ ለመደጋገፍ የሦስት ቀናት ውይይት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ተጀምሯል።

ሀገራቱ በህፃናት ጥቃት ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ተገቢውን አመራር በመስጠት እና ጥቃቱን ለማስቆም ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲሁም በብሔራዊ ደረጃ የህፃናት ጥቃትን ለመግታት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ እየተወያዩ ይገኛሉ።

በታምራት ደለሊ