የአፍሪካ ስታስቲክስ ዳይሬክተሮች ጉባኤ አዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል

ጥቅምት 14/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ስታስቲክስ ዳይሬክተሮች ጉባኤ በአፍሪካ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ላይ ያተኮረ አህጉራዊ ምክክር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በጉባኤው ላይ ተገኝተው ንግግር  ያደረጉት  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ምዝገባ ማከናወን መረጃን አደራጅቶ በዘመናዊ መንገድ ለመጠቀም ሚናው የጎላ  መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ መረጃን በዘመናዊ መልኩ አደራጅቶ ለመያዝ የተለያዩ ስራዎች እየሰራች እንደምትገኝ የጠቀሱት ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉባኤው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጋር ልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ነው ብለዋል።

በአፍሪካ በተለይም ከመረጃ ምዝገባ አያያዝ ጋር በተያያዘ ዘመናዊነትን ያልተከተለ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የጉባኤው ዋና ዓላማ የሁሉም አፍሪካዊያንን መረጃ በዘመነ መንገድ የሚመዘገብበትን አፍሪካ ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።

በኮንፈረንሱ የባለፉት ዓመታት የስራ ክንውኖች ተገምግመው ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ነው የተባለው።

በጉባኤው የተለያዩ ሀገራት የወሳኝ ኩነት ምዝግባ ሂደትና የአሰራር ተሞክሮዎች ቀርበው የልምድ ልውውጥ ይደረግባቸዋል።

በሱራፌል መንግስቴ