የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በዝግ እየመከረ ነው

ጥር 28/2014 (ዋልታ) 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ከሰዓት በዝግ በተለያዩ ጉዳዮች እየመከረ ነው፡፡

ጉባኤው ዛሬ ከሰዓት በሚኖረው መርሃ ግብር በአኅጉሪቱ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በተከናወኑ ሥራዎችና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ በዝግ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ያለበት ደረጃ በተመለከተ በሚቀርበው ሪፖርት በዝግ ውይይትና ክርክር እንደሚያደረግ ነው የወጣው መርሃ ግብር የሚያስረዳው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አፍሪካን ከጦር መሳሪያ ነፃ ለማድረግ ከዓመታት በፊት የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ አፈፃፀም ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መሪዎቹ እንደሚወያዩና አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ይጠበቃል::

የአፍሪካ ኅብረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በወሰዳቻቸው እርምጃዎችና በተገኙ ውጤቶች እንዲሁም ደቡብ አፍርካ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በሰራችው ሥራ ያስመዘገበችውን ተሞክሮ ለመሪዎች ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ የአኅጉሪቱን የኢኮኖሚ ውኅደት ለማፋጠንና በኮቪድ-19፣ በሰው ሰራሽና በተፈጠሮ አደጋዎች የተጎዳውን ኢኮኖሚ ፈጥኖ እንዲያገግም ለማስቻል የፋይናንስ ምንጮችንና አማራጮችን ለማሳደግ በሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ምክረ ሀሳብ ለመሪዎች ቀርበው ውይይትም ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡

እንደኢቢሲ ዘገባ ዛሬ ምሽት ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአፍርካ አገራት መሪዎች የእራት ግብዣ ያደርጋሉም ነው የተባለው፡፡