የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም 21 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚከበር ተገለጸ

መስከረም 18/2015 (ዋልታ) የኢሬቻ በዓል አከባበር በመላው አዲስ አበባ ከዛሬው እለት ጀምሮ እስከ መስከረም 21 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በዓሉ በዛሬው እለት በመላው አዲስ አበባ በፓናል ውይይቶችና ኤግዚቢሽኖች መከፈቱንም ተገልጿል፡፡

በነገው እለት መስከረም 19 ደግሞ በክፍለ ከተማ ደረጃ የፓናል ውይይት የሚደረግ ሲሆን መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም በማዕከል ደረጃ ከኦሮምያ ክልል ጋር በመቀናጀት የማጠቃለያ ፓናል ውይይት ይካሄዳል፡፡

በመስከረም 21 ቀን 2015 ዓ.ም የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል አከባበር በአባገዳዎች ብቻ እየተመራ የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢሬቻ የወንድማማችነት፤ እህትማማችነትና የምስጋና በዓል መሆኑንም የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢሬቻ፤ የኦሮሞ ህዝብ የጨለማውን ጊዜ አሳልፈን ብርሃን ያሳየኸንን ፈጣሪ እናመሰግናለን!! መሬቱን አረጠብክልን፤ ውሃው ሞላ፤ የደፈረሰው ጠራልን እናመሰግናለን! በማለት ለፈጣሪው ምስጋናውን የሚያቀርብበት ድንቅ በዓል መሆኑም ተመላክቷል፡፡