የኢሬቻ በዓል ዋዜማ የስፍራ ማፅዳት መርሀ ግብር በሆራ ፊንፊኔ ተካሔደ

መስከረም 19/2015 (ዋልታ) የኢሬቻ በዓል ዋዜማ በዓሉ የሚከበርበትን ስፍራ የማፅዳት መርሀ ግብር በሆራ ፊንፊኔ ተካሔዷል::

በፅዳት መርሀ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ከድር (ፒኤችዲ) እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል።

በመርሃግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የቂርቆስ ክፍለከተማ ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ከድር (ፒኤችዲ)  እንደተናገሩት ኢሬቻ የሰላም ተምሳሌት በመሆኑ ሁሉም ሰው ይህን የጋራ የሆነ በዓል በአንድነት እና በመቻቻል ሊያከብረው ይገባል ብለዋል፡፡

አክለውም ህብረተሰቡ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት እንቅስቃሴዎችን በትኩረት መከታተል ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሰላም የዘረጋችው እጇ የተነከሰባት ጊዜ በመሆኑ የውጪ ጠላት እና የውስጥ ባንዳ ሀይሎች ይህን የጋራ መሰብሰቢያችንን ጊዜ በመጠበቅ የግል አላማቸውን እንዳያሳኩ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ትኩረት ሰጥቶ ሊከታተል ይገባል ብለዋል፡፡

የዘመን መለወጫ፣ የመስቀል እና ሌሎች በዓላትን በጋራ ትብብራችን በሰላም እንዲጠናቀቅ እንዳደረግነው ሁሉ ለኢሬቻ በዓልም በጋራ መቆም ይኖርብናል ሲሉ ገልፀዋል።

በፅዳት ክንውኑ ላይ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ከሌሎች ክፍለከተሞች የተውጣጡ አዛውንቶች ወጣቶች እንዲሁም እናቶች ተሳትፈውበታል።

በግዛቸው ይገረሙ