የኢትዮጵያና አልጄሪያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብስባ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

መስከረም 2/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያና አልጄሪያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብስባ በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

አልጄሪያ የመድሐኒት ማምረትና ማከፋፈል (ፋርማሲዩቲካል) አወደ-ርዕይ በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደምታካሄድም ተነግሯል።

በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ከሬዲዮ አልጄሪያ ኢንተርናሽናል ጋዜጠኛ አሲያ ቤካር ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአልጄሪያ በነበራቸው ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወቅት ከአገሪቷ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ አገራት የቀጣይ ዙር የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብስባ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት የኮሚሽኑ ስብሰባ በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አምባሳደር ነቢያት ገልጸዋል።

በስብስባው ኢትዮጵያና አልጄሪያ በአየር የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ በጋራ ለመስራት ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

ስምምነቱ በሁለቱ አገራት መካከል ቀጥታ የአየር በረራ እንዲኖር በማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

በጋራ ኮሚሽኑ ስብስባ በኢትዮጵያና በአልጄሪያ መካከል በተለያዩ መስኮች የተፈረሙ ስምምነቶች ወደ ትግበራ ማስገባት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግም ነው አምባሳደሩ የገለጹ።

የሁለቱ አገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ለአራት ዙሮች ምክክር ማድረጉን አስታውሰዋል።

በተያያዘ አልጄሪያ የመድሐኒት ማምረትና ማከፋፈል (ፋርማሲዩቲካል) የምታስተዋውቅበት አወደ-ርዕይ በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አምባሳደር ነቢያት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አውደ-ርዕዩ በፋርማሲዩቲካል መስክ የተሰማሩ የአልጄሪያ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በዘርፉ ከተሰማሩ ተዋናዮች ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የአገራቱን ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።