የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱ ዳር እንዲደርስ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ጥር 3/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱ ዳር እንዲደርስ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል ሲሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት የሕወሓት ታጣቂዎች ለመከላከያ ሠራዊት ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ማስረከብ መጀመሩን አመልክተዋል። ይህም የሰላም ስምምነቱ መሬት መንካት መጀመሩን የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ያለ ምንም መስተጓጎል በጦርነቱ ለተጎዱት አካባቢዎች ሁሉ ባለው አቅም ልክ እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ መንግስት የአየር ትራንስፖርትን ጨምሮ መደበኛ አገልግሎቶች ስራ እንዲጀምሩ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

የተፈጠረውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ህገወጥ የታጣቂዎች ቡድን አባላት ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ በማሰብ ለፀጥታ ኃይሎች ከነትጥቃቸው እጅ እየሰጡ እንደሚገኙም አመላክተዋል።

ይህ በጎ ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋልም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ህገወጥ ታጣቂዎች መሣሪያቸውን አውርደው ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ህብረተሰቡም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

ከሰላማዊ ሁኔታዎች ሁሉም እኩል ተጠቃሚና አትራፊ ነው፤ የመላውን የህዝባችንን ችግሮችና ጥያቄዎች መቅረፍ የምንችለው አዎንታዊና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ስንችል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህ እውን እንዲሆን የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን ይገባናል ብለዋል፡፡