የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በየካ ክፍለ ከተማ የአረጋዊያን ቤት ዕድሳት አስጀመረ

የአረጋዊያን ቤት ዕድሳት

ሐምሌ 08/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በየካ ክፍለ ከተማ የአረጋዊያን ቤት ዕድሳት መርኃግብር አስጀመረ።

በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 አስተዳደር የአራት አረጋዊያን ቤት ዕድሳት ያስጀመሩት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራአስፈፃሚ ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል የአረጋውያን ቤት ማደስ የእያንዳንዱ ዜጋ እና የመንግስት ኃላፊነት መሆኑን ገልፀዋል።

ኮርፖሬሽኑ በዚህ ዓመት ለዚህ ተግባር አንድ ሚለየን ብር በመመደብ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረው፣ በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የሚታየውን የገቢና አኗኗር ልዩነት ለማጥበብ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

የአካባቢው ወጣቶችም በክረምት የተያዘውን ኢትዮጵያን የማልበስና በጎ አድራጎት ሥራዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በመርኃግብሩ የተገኙት የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራአሥፈፃሚ አቶ አስፋው ተክሌ በበኩላቸው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመረውን የቤት ዕድሳት መርኃግብር የእናቶችና አቅመ ደካማ ቤቶችን በማደስ ለነሱ ያላቸውን ድጋፍ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

በክፍለ ከተማ ደረጃ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 200 ቤቶችን ለማደስ ታቅዶ የ91 ቤቶች ዕድሳት መጀመሩን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ገልፀው፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽኑ ላደረገው አስተዋጽኦም አመስግነዋል።

በየካ ክፍለከተማ ወረዳ አንድ የዛሬውን ጨምሮ የ8 ቤቶች ዕድሳት በይፋ መጀመሩም ተጠቁሟል።

በዛሬው ዕለት የቤት ዕድሳት የተደረገላቸው አረጋዊያን ቤታቸው ዝናብ በሚሆንበት ጊዜ እንደሚያፈስ ገልጸው፣ በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ዕድሳት ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዛሬ በተካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ የቤት ዕድሳት መርኃግብር የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሠራተኞች፣ የክፍለ ከተማና ወረዳ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተገኝተዋል።

(በአድማሱ አራጋው)