የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር ለግማሽ ፍጻሜ አለፉ

ግንቦት 29/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማኅበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው ውድድር ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል።

በውድድሩ በምድብ ሁለት የተደለደሉት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ኔጄሩ በዩጋንዳ እግር ኳስ ማኅበር (ፉፋ) የቴክኒክ ማዕከል ዛሬ ከደቡብ ሱዳን ጋር ባደረጉት ጨዋታ 4 ለ 0 አሸንፈዋል።

አረጋሽ ካልሳ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርታለች። በውድድሩ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ወደ አምስት ከፍ አድርጋለች።

ሌላኛውን ግብ ሎዛ አበራ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረች ሲሆን የአጥቂ መስመር ተጫዋቿ እስካሁን በውድድሩ አራት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

ውጤቱን ተከትሎ ሉሲዎቹ በሰባት ነጥብ በታንዛንያ በግብ ክፍያ ተበልጠው ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፈዋል።

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመሩት ሉሲዎቹ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ሐሙስ ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት ከአስተናጋጇ አገር ዩጋንዳ ጋር ያደርጋሉ።

ብሔራዊ ቡድኑ በሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር ዛንዚባርን 5 ለ 0 ሲያሸንፍ ከታንዛንያ አቻው ጋር ሁለት አቻ መለያየቱ የሚታወስ ነው።

ዛሬ በምድብ ሁለት በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ ታንዛንያ ዛንዚባርን 12 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ምድቡን በሰባት ነጥብ በላይነት ማጠናቀቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የታንዛንያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ሐሙስ ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ከብሩንዲ አቻው ጋር ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ያደርጋል።

አራተኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማኅበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።