የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአህጉሪቷ ነጻ የንግድ ቀጣና መሳለጥ ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል – ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

ግንቦት 30/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በማስተሳሰር ለአህጉሪቷ ነጻ የንግድ ቀጣና መሳለጥ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ለአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጣና ውጤታማነት የአየር ትራንስፖርት ትስስር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል።

በአህጉሪቷ መካከል ያለውን የሰዎች እንዲሁም የሸቀጦች ማጓጓዝን በማሳለጥ ተመጋጋቢ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዝ የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለዚህ ደግሞ የአየር ትራንስፖርት ትስስር ሚናው ከፍተኛ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አህጉሪቷን በማስተሳሰር የአፍሪካ መሪዎች የወጠኑትን አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ውጤታማነት ሚናውን አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡

አየር መንገዱ በአፍሪካ ያሉትን መዳረሻዎች እያሳደገ በአሁኑ ወቅት ወደ 64 የአፍሪካ ከተሞች በረረ እንደሚያደርግ የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህም አየር መንገዱ አብዛኛውን የአፍሪካን ሀገራት በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ተግባሩን እያፋጠነ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

በጥቂት ጊዜ ውስጥም አየር መንገዱ የቀሩትን ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ሥራ እየሠራ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአፍሪካ ህብረት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር መጋቢት 2018 በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ባካሄደው የመሪዎች ጉባኤ የተሳተፉ 44 የአፍሪካ አገሮች የአህጉሪቷን ነጻ የንግድ ቀጣና እውን ለማድረግ መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

ስምምነቱም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ጥር 1 ቀን 2021 ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ በአየር መንገዷ በኩል በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚጓጓዘውን የመጀመሪያ ጭነት ከኤስዋቲኒ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት እንዲጀመር አድርጋለች፡፡

ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግም በ2034 በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በ60 በመቶ በማሳደግ በመካከላቸው ያለውን የሸቀጦች የንግድ ታሪፍ በ90 በመቶ እንደሚያስቀርም ነው የሚገለጸው፡፡ ይህም የአህጉሪቱን የ3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ዓመታዊ ምርት ድርሻ እንደሚኖረውም ታውቋል፡፡