የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው እለት ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ ጀመረ

ታኅሣሥ 19/2015 (ዋልታ) መንግስት በገባው ቃል መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው እለት ወደ መቀሌ ዳግም መደበኛ በረራ ጀመረ።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ዛሬ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መንገደኛችን ጭኖ ወደ መቀሌ አምርቷል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ አየር መንገዱ ወደ መቀሌ ዳግም በረራ መጀመሩ መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑም ተገልጿል፡፡

መንገደኞቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አየር መንገዱ ወደ መቀሌ ዳግም በረራ በመጀመሩ መደሰታቸውን ጠቅሰው ይህም መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ትላንት በሰጡት መግለጫ ወደ መቀሌ ዳግም በረራ መጀመሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። ይህም የእርስ በርስ ግንኙነቱን በማጎልበት የሰላም ሂደቱን ያጠናክራል ብለዋል፡፡

ከቀናት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ልኡክ ወደ መቀሌ በማቅናት እነዚህና መሰል አገልግሎቶችን ማሳለጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከህወሃት አመራሮችና ከመቀሌ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።