የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ6.6 በመቶ እንደሚያድግ ተገለጸ

ግንቦት 2/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ በ6 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚያድግ ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም አመላካች መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጹ።

የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት የኢትዮጵያ የ9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባሉበት ገምግሟል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የአፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፤  የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን  ጨምሮ አለም አቀፋዊ ጫናዎችና  በአገር ውስጥ የተከሰተው ድርቅ  ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚው ፈተናዎች እንደነበሩ አመላክተዋል።

ዩክሬንና ሩሲያ በአፍሪካ ከፍተኛውን የስንዴና ዘይት ምርቶች እንደሚያቀርቡ የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ አፍሪካ 73 በመቶ የሚሆነውን የዘይት ምርት ከሁለቱ አገሮች እንደምታስገባም አስታውሰዋል።

የሁለቱ አገራት ጦርነትም የምግብ ሸቀጦችን ጨምሮ ነዳጅና ሎሎች መሰረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲንር ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ለአብነትም አንድ ቶን ቤንዚን በኅዳር ወር ከነበረበት 870 ዶላር አሁን ላይ 1 ሺህ 28 ዶላር፤ እንዲሁም አንድ ቶን ጋዞሊን ከነበረበት 730 ዶላር  ወደ 1 ሺህ 138 ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

መንግስት 85 በመቶ የሚሆነውን የነዳጅ ጭማሪ በድጎማ መልክ በራሱ ወጪ እየሸፈነ መሆኑንም አብራርተዋል።

የስንዴና የዘይት ዋጋ በጥርና መጋቢት ወራት ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 65 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን ገልጸው፤ ይህም በኢትዮጵያ ገበያ ላይ የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ማዳበሪያ ከሁለት ዓመት በፊት በአንድ ቶን ከነበረበት የ250 ዶላር ዋጋ አሁን ላይ ወደ 1 ሺህ 300 ዶላር ከፍ ማለቱንም ጨምረው  ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ አገራት ጦርነት ምክንያት በአጠቃላይ መንግስትን እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ እስከ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጣ እንደሚያደርገውም ነው ያነሱት፡፡

ነገር ግን መንግስት በተለይ በግብርና፡ ማእድንና አገልግሎት ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተጠቀሱትን ዓለም አቀፋዊና በአገር ወስጥ የተከሰተውን ድርቅ ተቋቁሞ ውጤት አስመዝግቧል ነው ያሉት፡፡

በግብርናው መስክ 336 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰው፣ ከዚህም ውስጥ የበጋ መስኖ ልማትን ጨምሮ 25 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ መመረቱንም አንስተዋል፡፡

ይህም በተለይ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተከሰተው የስንዴ ዋጋ ንረት በኢትዮጵያ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መከላከል መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከውጪ ንግድ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ጠቁመው ከአገልግሎት ዘርፍም 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ  ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

በሌሎች ዘርፎች ላይም የተሻለ አፈጻጸም በመኖሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ በ6 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚያድግ ያመላክታል ብለዋል፡፡፡

በአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የዋጋ ግሽበትን ለመቋቋም የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትሯ ጥሪ ማቅረባቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ዜጎች ሰላምና ጸጥታ በማስከበር የድርሻቸውን በመወጣት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር አስተዋጥኦ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል፡፡