የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ነገ ከታንዛኒያ አቻው ጋር ይጫወታል

                                                     ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን

ጥር 26/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ነገ ከታንዛኒያ አቻው ጋር ለሚያደርገው የ2022 ዓለም ዋንጫ 4ኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

ቡድኑ በኮስታሪካ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ 4ኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን እያደረገ ነው።

የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ለውድድሩ የነበረውን አጠቃላይ ዝግጅት በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከታንዛኒያው ሽንፈት ብዙ ነገር ተምረናል ያሉት አሰልጣኝ ፍሬው ቡድኑ በጠባብ ውጤት ተሸንፎ መመለሱን ተከትሎ ውጤቱ የሚቀለበስ በመሆኑ የተሻለ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።

ቡድኑ ከጨዋታው በፊት በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ የመጨረሻ ልምምድ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከታንዛንያው የመጀመሪያ ጨዋታ መልስ ጠንካራ ዝግጅቱን ሲያደርግ እንደቆየና በዛሬው ዕለትም ቀለል ያለ ልምምድ እንዳደረገ ነው የተገለጸው፡፡

በልምምድ መርኃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች ማኅበር ተገኝተው ቡድኑን በማነቃቃት መልካም ዕድል ተመኝተዋል።

ቡድኑ በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ባዛንዝባር ላይ ጥር 15 በታንዛኒያ አቻው 1 ለ 0 መሸነፉ ይታወቃል፡፡

የመልሱ ጨዋታ ነገ 10:00 በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋል። በደርሶ መልስ ውጤቱ አሸናፊው ቡድን ከጋና እና ከዩጋንዳ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።

በመሰረት ተስፋዬ

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://www.facebook.com/waltainfo

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!