የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ም/ቤት አባላት የሕዳሴ ግድብን ጎበኙ

መስከረም 30/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አባላት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጎበኙ።
የምክር ቤቱ ልዑክ ኑሯቸውን በለንደን ባደረጉት ኢትዮጵያዊ በአቶ አለባቸው ደሳለኝ መሪነት በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ የሚታወቅ ነው።
ይህ ልዑክ ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ በሁለንተናዊ መልኩ ማጠናከር እንዲችል ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተወያየ ሲሆን፣ በቆይታውም የተለያዩ ጉዞዎችና ጉብኝቶችን ያደርጋል ተብሏል።
በዚሁ መሰረት ልዑኩ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ፕሮጀክት የሆነውን የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ጎብኝቱን እያደረገ ነው።
የዛሬውን ጉብኝት ያደረጉት የዳያስፖራ አባላት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ ማየት የቻሉ ናቸው።
በቀጣይ የልዑኩ ቆይታ ሌሎች አባላት ፕሮጀክቱን እንደሚጎበኙ ኢዜአ አስነብቧል።