የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል በመላ ኢትዮጵያ በሰላም መጠናቀቁን ገለፀ

ሐምሌ 2/2014 (ዋልታ) የ1443ኛው ዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በመላው ኢትዮጵያ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለፀ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሕዝቡን ከጎኑ በማሰለፍና ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በዓሉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የሕዝቡን ፀጥታና ደኅንነት የማስከበር ሥራውን በብቃት ተወጥቷል ብሏል።

በጥበቃው ላይ የተሰማሩት የፖሊስ ሰራዊት አባላት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ከራሳቸው በፊት ሕዝቡን በማስቀደም የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት በመወጣት የታለመውን ግብ ማሳካቱንም ነው የገለጸው።

ከፖሊስ የተሰጠውን መግለጫ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የፀጥታና ደኅንነት አካላት ላደረጉት ቀና ትብብርና ድጋፍ ፖሊስ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

እንዲሁም ለዚህ ስኬት የበኩላችሁን ድርሻ የተወጣችሁ የእስልምና እምነት ተከታዮችና የሃይማኖት አባቶች፣ በዓሉን ያስተባበራችሁና የመራችሁ ወጣቶች፣ ላደረጋችሁት ከፍተኛ ትብብር የኢትየጵያ ፌዴራል ፖሊስ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ምስጋና አቅርቧል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW