የኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ካውንስል 2ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

የኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ካውንስል ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ “ምሁራኖቻችን ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ግቦች” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ሀገሪቱን ወደምንፈልገው ደረጃ ለማድረስ የኢትዮጵያውያን ሙሉ ፕሮፌሰሮች ድርሻና ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለንበት ቦታና ደረጃ ላይ ሆነን ተሰናስለን ከሰራን ሀገሪቱ ወደምትፈልገው የእድገት ደረጃ እናደርሳለን ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ በኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና ላይ ስኬት ለማምጣት ፕሮፌሰሮች ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ጉባኤ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ግቦች ስኬት ከፕሮፌሰሮች ምክር ቤት በሚጠበቁ ድጋፎች ላይ ይመክራል፡፡

ዝግጅቱ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ የችግኝ እንክብካቤ በማድረግ የተጀመረ ሲሆን  የዩኒቨርሲቲውን ላቦራቶሪዎች፣ ሰርቶ ማሳያዎችና የልህቀት ማዕከላት ይጎበኛሉ ተብሏል።

በነገው ዕለትም በሚኒስቴሩ የትኩረት መስኮች እና ከኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ምክር ቤት በሚጠበቁ ድጋፎች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

ከሚኒስቴሩ ምክር ቤቱን ሲመሰርት ዋና ዓላማው ኢትዮጵያውያን ባለሙሉ ፕሮፌሰር ምሁራን ከከሚኒስቴሩ ጋር በመቀናጀት የሳይንስ፣ ከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ግቦችን ለማሳካትና በሀገር ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መንገድ ለመፍጠር መሆኑን ከከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።