የኢትዮ – ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኃይል መስጠት ሊጀምር ነው

ጥቅምት 11/2015 (ዋልታ) የኢትዮ – ኬንያ ባለ500 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ኃይል ማስተላለፍ ይጀምራል።

ህብረተሰቡ ከኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ንክኪ እንዲርቅም ተጠይቋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኮንስትራክሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ክብሮም ካህሳይ ከወላይታ ዞን አስተዳዳሪና የመምሪያ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ ለሁለቱ ሀገራት የኃይል ትስስርና ለኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ለአመራሮቹ ገልፀውላቸዋል፡፡

በተመሳሳይ በጋሞ ዞን በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀመው ስርቆት እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም ክትትል የሚያስፈልገው ስለመሆኑ ለአመራሮቹ ተገልጾላቸዋል፡፡

በቀጣይም በዞኑ መሰረተ ልማቱ በሚያልፍባቸው አካካቢዎች ምንም ዓይነት ስርቆት እንዳይከሰት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንዲሰራ፣ የፀጥታ አካላትም ተንቀሳቅሰው እንዲጠብቁና ህብረተሰቡ በይዞታው ላይ የተተከሉትን ምሰሶዎች እንዲጠብቅ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንዲሰራ ጥያቄ ቀርቦ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ 18 ቤቶች ካሳ ተከፍሏቸው አለመነሳታቸው በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ህብረተሰቡም መስመሩ ኃይል ያልተለቀቀበት መስሎት በመዘናጋት ጉዳት እንዳይደርስበት በህዝብ መድረክ፣ በማህበራዊ ሚዲያና ለነዋሪዎች ተደራሽ በሆኑ ዋና ዋና ሚዲያዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንዲሰራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በተያያዘ ዜና በፕሮጀክቱ ሥራ መጀመር ዙሪያ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተመሳሳይ ውይይት መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል።