የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ማሳደግ በዘርፉ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑ ተገለጸ

ታኅሣሥ 2/2014 (ዋልታ) የኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ በዘርፉ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

በሞጆ ከተማ የሚገኙ የቆዳ ኢንዱስትሪዎችን የጎበኙት ሚኒስትሩ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ የግል ሴክተሮችን በቅርበት መደገፍ እና ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በከተማዋ ከሚገኙ 27 ያህል መካከለኛ እና ከፍተኛ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 19 የሚሆኑት የተሻለ ምርት እያመረቱ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ በከተማዋ ከሚገኙ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች 90 ሚሊየን ዶላር ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ ባለፉት አምስት ወራት የእቅዳቸውን 73 በመቶ ማሳካት መቻላቸውንም ጨምረው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ በዘርፉ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡