የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢ-ሰርቪስ አገልግሎትን አስጀመረ

ሐምሌ 26/2014 (ዋልታ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ማስጀመሪያ ስምምነት ተፈራርሟል::

ከዘመኑ ጋር መራመድ የሚያስችል ቀልጣፋ እና ተደራሽ አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ የቀጣይነትና የእድገት መንገድ የሚጠርግ ነው ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ይህን ታሳቢ በማድረግም ከብልሹ አሰራር የፀዳ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመፍጠር በሚኒስቴሩ የአሰራር ስርአትን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል::

በዚህም የኢ-ሰርቪስ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትን አስጀምሯል:: የኢ-ሰርቪስ አገልግሎትም የገበያ ትስስርን በመፍጠር የግሉን ዘርፍ ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት በማሳደግ ከውጤት እንዲወዳጅ ከማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተገልጿል::

እንደ ሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየተደረገ ያለውን ርብርብ ከመደገፍ አኳያ የበኩሉን አስተዋጽዖ ያበረክታል የተባለለት የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት አሰጣጥን ተግባራዊ በማድረግ በአገልግሎት እና ተገልጋይ መካከል ያለውን እንግልት የሚቀንስም ይሆናልም ነው የተባለው::

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደ ሀገር የጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት መርኃ ግብርን በመረጃ በመደገፍ እና ተቋማዊ ቅንጅትን በመፍጠር ዘርፉ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፍ ከማድረግ ረገድ አስተዋጽዖው የጎላ ይሆናል ተብሏል::

በሔብሮን ዋልታው