የእብናት ወረዳ ዘማቾች ሽኝት ተደረገላቸው

የእብናት ወረዳ ዘማቾች

ጥቅምት 25/2014 (ዋልታ) የደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ ነዋሪዎች የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ተቀብለው አሸባሪውንና ወራሪውን ሕወሓት ለመፋለም ወደ ጦር ግንባር እየዘመቱ ነው።

ወደ ግንባር ሽኝት የተደረገላቸው ዘማቾች እጅግ ከፍተኛ የማሸነፍ ወኔ፣ ሥነ ልቦና፣ ጀግንነት እና ቁጭት ይነበብባቸዋል።

ዘማቾቹ እንደገለጹት አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ ሊበቃ ይገባል፤ ከእንግዲህ በኋላ የአሸባሪውን ኃይል የሚሸከም ትከሻ የለንም፤ አርሶ ማምረትና ወልዶ ማሳደግ የሚቻለው የአሸባሪውና ወራሪው ኃይል ግብዓተ መሬት ሲፈጸም ብቻ ነው፡፡

ወራሪ እና ሽብርተኛ ኃይል በአጭር ጊዜ ድባቅ በመምታት ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ነፃ ለማውጣት ምለው ተገዝተው መነሳታቸውንም አብራርተዋል።

ነፃነቷን ጠብቃ ለዘመናት የኖረችውን ኢትዮጵያ በጡት ነካሹና አሸባሪው የሕወሓት ኃይል ተወራለች፤ ሕዝቡ ከጫፍ እስከጫፍ በአንድነት ከተነሳ ግን አሸባሪ ኃይሉን በአጭር ቀን መደምሰስ ይችላል፤ ለዚህም በነቂስ ተነስተናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የእብናት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሙሉጌታ ይማም ነጻነቷ፣ ሉዓላዊነቷ እና ክብሯ የተጠበቀ ሀገር ከአያቶቻችን እንደተረከብን ለሚቀጥለው ትውልድም ከነነጻነቷ፣ ሉዓላዊነቷ እና ክብሯ ነው ልናስረክብ የሚገባው ብለዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው ሕዝቡ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ተፋልሞ ነጻ እንዳይወጣ የሐሰት ወሬ በሚያናፍሱ የውስጥ ባንዳዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ ይወሰዳል፤ እንዲህ ዓይነት ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላትም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።