የኦንላይን አገልግሎት ክፍያዎች በዲጂታል አማራጭ እንዲፈፀሙ ሊደረግ ነው

መጋቢት 23/2014 (ዋልታ) የኦንላይን አገልግሎት ክፍያዎች በዲጂታል አማራጭ እንዲፈፀሙ ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በሚቀጥለው ሳምንት የሚጀምረው አገልግሎቱ ዜጎች ከውጭ አገራት ጭምር ባሉበት ቦታ ሆነው ለተጠቀሙት የመንግሥት አገልግሎት በማስተር ካርድ የክፍያ አማራጭ ክፍያዎችን በኦን ላይን መክፈል ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የትግበራ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅት አባላት ይህንን የክፍያ መተግበሪያ አማራጭ በመጠቀም ፍቃድ ለማውጣትና ለማደስ በማንኛውም የክፍያ ካርድ አይነት ክፍያ መፈፀም እንደሚጀምሩ ተገልጿል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ማስተርካርድ የመንግሥት አገልግሎት የክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን የሚያስችላቸውን ሰምምነት አድርገዋል፡፡

ስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የማስተርካርድ የክፍያ አማራጭን ከኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ፖርታል ጋር በማቀናጀት ዜጎች ክፍያዎችን በኦንላይን እንዲፈፀሙ ያስችላቸዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጥረታችን ኢትዮጵያን ከጥሬ ገንዘብ ህትመትና ስርጭት ወጪ ማላቀቅና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂያችን ተግባራዊ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

የማስተር ካርድ የምስራቅ አፍሪካ ሥራ አስኪያጅ ሸርያር አሊ ቀልጣፋ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ፈጠራ የታከለበት የዲጂታል የክፍያ አማራጮችን በመዘርጋት የኢትዮጵያ መንግሥትን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንደሚደግፉ መናገራቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ይህንን አሰራር ለመተግበር ማስተር ካርድ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስምምነት ላይ የደረሱት በ2020 ሲሆን ይህም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቲጂን” መሰረት በማድረግ ነው ተብሏል።

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!